ሕብረት ባንክ እና አሐዱ ባንክ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ
ሕብረት ባንክ እና አሐዱ ባንክ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የአጋርነት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በሕብረት ባንክ ዋና መ/ቤት ተፈራርመዋል፡፡
ሕብረት ባንክ ቴክኖሎጂን ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው በማስተዋወቅ ረገድ ቀዳሚ ባንክ ሲሆን ሕብር ኢ-ኮሜርስን የተሰኘውን አገልግሎት ለንግዱ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና ነጋዴዎች በማስተር ካርድና በሌሎች አለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ካርዶች በመጠቀም ክፍያቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ ደንበኞች መቀበል እንዲችሉ ለማድረግ አስችሏል፡፡
ዛሬም በሕብረት ባንክና በአሐዱ ባንክ መካከል የተፈረመው ስምምነት አሐዱ ባንክ ላለመው የክራውድ ፈንዲንግ (crowd funding) ፕሮግራም የሕብረት ባንክን የኢ-ኮሜርስ ፕላትፎርም በመጠቀም በዓለም ዓቀፍ ካርዶች በኩል ከውጭ ሀገር ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ነው፡፡
ሕብረት ባንክ እንደስሙ በሕብረት ሰርቶ በሕብረት ማድግን መርሁ አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ከአጋር ባንኮች ጋር የተለያየ ይዘት ያላቸው የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም፣ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ እና የጋራ አቅምን አብሮ በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሕብረት ባንክ ከአንበሳ ባንክ እና ከዘምዘም ባንክ ጋር ያደረጋቸው የትብብር ስምምነቶች እንደ ማሳያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሕብረት ባንክ ከአሐዱ ባንክ ጋር የተፈራረመው ስምምነት በአጋርነት አብሮ መስራት ከማስቻሉም በላይ ከውጭ ሀገር የሚላከው ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግና ለሀገር ኢኮኖሚ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡
በቀጣይም ሁለቱ ባንኮች በጋር ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ሥራዎች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ሕብረት ባንክ!
በሕብረት እንደግ!