ሕብረት ባንክ ከኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበረከተለት
ሕብረት ባንክ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ድጋፍ የሚሹ አንጋፋ አትሌቶችን ለመደገፍ በሚያደርው ጥረት አሻራውን እያኖረ በመሆኑ ከኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሚያዝያ 22/2014 ዓ/ም አራት ኪሎ በሚገኘው ወ.ወ.ክ.ማ. በተካሄደው ስነስርዓት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን በቀለ ሕብረት ባንክ ኢትዮጵያን በአለም አደባባይ ያኮሩ አንጋፋ አትሌቶች በህይወት እያሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ እገዛ ማድረጉ እንደሚያስመሰግነው ገልጸዋል፡፡
ሕብረት ባንክን በመወከል የምስጋና የምስክር ወረቀቱን የተቀበሉት የሕብረት ባንክ ቢዝነስና ኦፕሬሽንስ ሲኒየር ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ በበኩላቸው መድረኩ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ እና ከአትሌቶች ጋር ለመተዋወቅ ብሎም ጥብቅ ትስስር ፈጥሮ በቀጣይ የሚከናወኑ የአጋርነት ስራዎችን ለማሳለጥ የሚያግዝ ታላቅ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም አንጋፋና ተተኪ አትሌቶች የታደሙ ሲሆን የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ለሀገራቸው የላቀ አስተጽኦ ላበረከቱት ለአትሌት ንጋቷ ወልዴ ለአትሌት ባሻ ሀይሉ አበበ ለአትሌት ገረመው ደንቦባ ለአትሌት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ እንዲሁም ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘብይደር ዘውዴ የክብር ካባ እና የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡