ሕብረት ባንክ ጠቅላላ ሃብቱን ወደ 113.93 ቢሊዮን ብር አሳደገ



ሕብረት ባንክ ጠቅላላ ሃብቱን ወደ 113.93 ቢሊዮን ብር አሳደገ
ሕብረት ባንክ 28ኛውን መደበኛ እና 14ኛውን አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሂዷል፡፡
የሕብረት ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ተሰማ ለጉባኤው ባሰሙት ሪፖርት ባንኩ በበጀት ዓመቱ በብዙ መመዘኛዎች ጠንካራ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደቀረበው የሕብረት ባንክ ጠቅላላ ሀብት ከፍተኛ እድገት በማሳየት 113.93 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17.96 በመቶ ወይም የ17.35 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ባንኩ የደንበኞቹን ቁጥር በማሳደግ እና የአገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 92.68 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ18.03 ቢሊዮን ብር ወይም የ24.16 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ታውቋል፡፡ ከወለድ ነፃ ፋይናንስን ጨምሮ አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት 79.33 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በበጀት አመቱ የባንኩ አጠቃላይ ገቢ ወደ 16.74 ቢሊዮን ብር ማደጉንና ይህም ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የ26.55 በመቶ ወይም የ3.51 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝትም ካለፈው አመት የ47.4 በመቶ ወይም የ96.49 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ በማሳየትም 300.11 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከግብር በፊት የ749.04 ሚሊዮን ብር ትርፍ መገኘቱን እና ይህም የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ከመወሰኑ ጋር በተገናኘ ባንኩ ያጋጠመውን ተግዳሮት በመቋቋም ጥንካሬውን ያረጋገጠበት መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን በቀጣይም ወቅቱ የሚጠይቀውን የአሰራር ለውጥ በመተግበር እንዲሁም ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመለወጥ ሕብረት ባንክ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ሕብረት ባንክ
በሕብረት እንደግ!