የሕብረት ባንክ ሰራተኞች የሰራተኞች ቀንን አከበሩ፡፡
የሕብረት ባንክ ሰራተኞች ’’የሕብረት ቀን’’ በሚል መሪ ቃል አመታዊ የሰራተኞች ቀንን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ/ም በድምቀት አክብረዋል፡፡ በዋናው መስሪያ ቤት እና አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ቅርኝጫፎች የሚሰሩ ሰራተኞች በዓሉን አዲስ አበባ በሚገኘው ጎልፍ ክለብ ያከበሩ ሲሆን፤ በክልል ከተሞች የሚገኙ ሰራተኞችም በተመሳሳይ ቀን በአሉን አክብረዋል፡፡ በበአሉ ላይ በተለያየ ጊዜ የባንኩ ሰራተኞች የነበሩና አሁን በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ የባንኩ ሰራተኞችን ጨምሮ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፤ የስራ አመራር አባላት እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በዓሉን በንግግር የከፈቱት የሕብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ የባንኩ ትልቅ ሀብት ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጸው ሰራተኞች በኮቪድ ወረርሺኝና በተጨማሪም በጦርነት ወቅት የፋይናንሱ ዘርፍ የገጠመውን ፈተና በድል በመወጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የሕብረት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ኢንጅነር ሳምራዊት ጌታመሳይ በበኩላቸው የሰራተኞች ቀን መከበር በሰራተኞች መካከል የተሻለ ግንኙነት ከመፍጠር ባለፈ ለአንድ አላማ ለመቆም ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለባንኩ ስኬታማነት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ለእድለኞችና ለስነ ጽሁፍ ውድድር አሸናፊዎች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ፈተና ተቋቁሞ የባንኩን ሰራተኞች ሀብት እና ስም እና ዝና ጠብቆ ከማቆየት አንጻር ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ለሰሜን ዲስትሪክትም እውቅና ተሰጥቷል፡፡
ሕብረት ባንከ
በሕብረት እንደግ!