የሕብረት ባንክ አመራሮች እና ሰራተኞች ደም ለገሱ

የሕብረት ባንክ አመራሮች እና ሠራተኞች የባንኩን 25ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልን አስመልክቶ የሕብረት ቤተሰብ የደም ልገሳ በሚል ስያሜ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም-  በባንኩ ዋና መ/ቤት የደም ልገሳ መርኀ ግብር አከናውነዋል፡፡ 

በመርኀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕብረት ባንክ የቢዝነስ እና ኦፕሬሽንስ ሲኒየር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን  ሲወጣ መቆየቱን እና በዚህም ረገድ ባንኩ እንደባንክ ከሚያደርጋቸው ሰፊ ድጋፎች በተጨማሪ የመደጋገፍ ባሕልን በማስረጽ የባንኩ ሠራተኞችም በየወሩ ከደሞዛቸው በማዋጣት የተለያዩ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችን እንደሚደግፉ ገልጸው   ደምን ለግሶ በደም እጦት የሞት አፋፍ ላይ የነበረን ሰው  መታደግ ትልቅ እድል መሆኑና ባንኩ የቆመለትን በሕብረት የማደግ መርህንም በተዓባር የሚያሳ ነው ብለዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ተወካይ ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ በበኩላቸው ሕብረት ባንክ ከሚሰጠው የባንክ አገልግሎት ባሻገር  ሰራተኞቹንም ጭምር በማሳተፍ የሚሰራቸውን የበጐ አድራጐት  ሥራዎች  አድንቀዋል፡፡ 

ከ4ዐኛ ጊዜ በላይ ደም የለገሱት የባንኩ ሠራተኛ አቶ መርሻ ታደሰ ተገኝተው ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ደም መለገስ ከአድሎ የጸዳ ልዩ ስጦታ መሆኑን  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መርኀ ግብሩ የባንኩ አመራሮችንና ሰራተኞችን ብቻ ሳይሆን ፈቃደኛ የሆኑ ሌሎች ግለሰቦችንም ተሳታፊ እንዲሆኑ የጋበዘ ነበር፡፡

Similar Posts